የቀቤና ወረዳ ታሪካዊ መዳረሻዎች
ታሪካዊ የቀቤና ወረዳ መዳረሻዎች
የዳንሼ ሀድራ
የዳንሽይ ሀድራ ከአ.አ 142 ኪሜ በማእከላዊ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በ ፈረጀቴ ቀበሌ ከወልቂጤ 8 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል።ይህ ሀድራ በልዩ ወረዳው ከሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ከሆኑ ቀደምት ሀድራዎች መካከል አንዱ ሲሆን እኢአ በ 1909 የዛሬ 118 ዓመት በታዋቂው ሙፍቲ እና ዓሊም ሼህ በሽር ሀሰን እንደተመሰረተ ይነገራል።በአንድ ወቅት ሀድራው ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የእውቀት እና የልህቀት ማዕከል የነበረ ሲሆን በርካታ ዓሊሞችን እና ሙህራንን ያፈራ ተቋም እንደ ነበረ በአፈ ታሪክ ከሚነገረውም በላይ አሁን በውስጡ የሚገኙ ጥንታዊ መዛግብቶች እና የፅሁፍ ማስረዎች ህያው ምስክር ናቸዉ ።በማዕከሉ በርካታ የፊቂህ፣የተውሂድ፣የተፍሲር እና መንጢቅ እና ነህው(የአረብኛ ሰዋሰው) በእጅ የተፃፉ ጥንታዊ መዛግብቶች የሚገኙ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከትላንት እስከ ዛሬ ያለውን የቀቤና ህዝብ አሰፋፈር እና ታሪክ እንዲሁም እንደ ፈትሁል ሀበሻ የመሳሰሉ የታላላቅ ታሪካዊ መዛግብቶች መገኛም ማዕከል ነው።ይህንን ሀድራ መጎብኘት መንፈስን ሀሴትን ያጎናፅፋል።
ቢሞላ መካነ ቅርስ
ዘቢሞላ በማ/ኢ/ክ በቀቤና ልዩ ወረዳ የሚገኝ ጥንታዊ መስጊድ ሲሆን ከወልቂጤ 1.5 ኪ.ሚ ርቀት ላይ የሚገኝ ኢስላማዊ ማዕከል ነው።እድሜ ጠገብ የሆነው ዘቢሞላ በአገራችን አስደናቂ ከሚባሉ ኢስላማዊ የቅርስ ስብስቦች አንዱ እና እጅግ ታሪካዊው ሥፍራ ነው። የመሰረቱትም የታላቁ አሊም ሼህ ሡሩር ሼህ በሺር (ኦቢዩ) ናቸው።ኦቢዩ ውልደታቸው ልዩ ስሙ ዘናበነር በተባለ ስፍራ እንደሆነ ይነገራል።ይህንን የዘቢሞላ ማዕከል በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1905 ነው።ዘቢሞላ የሚለውን ስያሜ ያገኘው ከቀቤንኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም የመድኃኒት አምባ ማለት እንደሆነ ይወሳል። ስያሜውንም ሊያገኝ የቻለው ስፍራው ላይ የተለያዩ ፈዋሽ ዕፅዋት ስለሚገኙ መሆኑ ይነገራል። በማዕከሉ ውስጥ እስከ 109 ዓመታት እድሜ ያስቆጠሩ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች በብዛት ይገኙበታል።ዘቢሞላ ከምስረታ ጀምሮ ስሙ ገኖ የወጣበት ምክንያት ትልቅ የእስልምና እምነት እና የትምህርት ማዕከል በመሆኑ የተነሳ ነው። ለኢስላማዊ ትምህርት በመጡ ደረሶች ብዛት፣እንግዶች፣የመውሊድ ክብረ በአል እንዲሁም የረመዳን ፆም መንፈሳዊ ክዋኔዎች ዘቢሞላን በደማቅ ድባብ ከፍ እንዲል ያደርጉታል።ማዕከሉ በየ ዓመቱ በመደበኛነት ከ120-450የሚደርሱ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል።
የዘቢሞላ ሌላው መገለጫው የቅርስ ማዕከልነቱ ነው ለጥናትና ምርምር አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ የፅሁፍ ቅርሶችን ከ 1500 እስከ 2000 የሚደርሱ የፅሁፍ ቅርሶች (ልዩ ልዩ ታሪካዊ መፅሐፍቶች፣ በብራና የተፃፉ ቁርዓኖች እና ኪታቦች) ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የጦር መሳሪያዎች(ጦሮች ፣ጋሻዎች እና ጎራዴዎች ) እንዲሁም 122 ዓመታትን ያስቆጠረ እድሜ ጠገብ መስጂድ በማዕከሉ ውስጥ ይገኛል።ዘቢሞላ 4 ትውልድን ያስተናገደ ገናና ስፍራ ይምጡ ይጎብኙ፤: