ማረቆ ልዩ ወረዳ ባሀላዊ
በማረቆ ልዩ ወረዳ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባሀላዊ ተብለው የሚመደቡ በርካታ የቱሪስት መስህብ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡
ራጋ_ማጋ
የማረቆ ብሄረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የተጀመረው በጥንት ዘመን እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡ የባህላዊ ዳኝነት ስርዓት መጠሪያ ስም ‹‹ሊቢደን ሀፋን ዱሚቾ“/”ሜጢ ሀፋን ሴራ›› ይባላል፡፡ የሊቢዶ ማረቆ ብሄረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ራጋ ማጋ በመባልም ይታወቃል። ማጋ የመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ሲሆን ግጭቱን የሚዳኙትም ሰዎች ማጋ ተብለው ይጠራሉ።ማጋ ሆነው የሚመረጡ ሰዎች ሶስት መስፈርቶችን ሊያሟሉ ይገባል። ሜሮ ሴራን ማወቅ፣ ጢሮ/ግፍ/ እና ፈሮን ጎልግሎ ማውጣት መቻል፣ ወገንተኛ ያልሆነ መሆን አለበት።ማጋዎች፣ ተጋጪዎች እና የክሱ ታዳሚዎች በግጭት አፈታት ስረዓቱ ወቅት ስፍራው ላይ ይገኛሉ።ራጋ አንድ ሰው ሲሆን በእድሜ ቆይታ ቀድመው ከነበሩት ራጋዎች(ማጋዎች) ልምድ ያካበተና ግጭትን መፍታት የሚችል ሰው ነው። ራጋ በሊቢዶ ማረቆ የግጭት አፈታት ስርዓት የመጨረሻ የፍርድ አሰጣጥ ስረዓት ነው። ራጋ የሚመረጠው በማጋ ሲሆን ትኩረት ተሰጥቶት መመረጥ አለበት። ይህ የስልጣን እርከን በዘር አይተላለፍም።በሊቢዶ ማረቆ የግጭት አፈታት ስረዓት ራጋ ማጋ የሚዳኙ አካላት በዳዩም ሆነ ተበዳዩ በተሰጠው መፍትሔ ወይም ውሳኔ ላይ ካልተስማሙ ያልተስማማው አካል ጌፈቻ/ይግባኝ/ መጠየቅ ይችላል።ይህ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት የሚካሄድበት ቦታ ልዩ መጠሪያ ስሙ ቆሼ ተብሎ ይጠራል።